አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፈረንጆቹ መጋቢት 2023 ጀምሮ ከ58 ሀገራት እና ግዛቶች በ38ቱ 153 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ለምግብ ዋስትና ችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ የምግብ ዋስትና መረጃ መረብ ዓመታዊ ሪፖርት አመላከተ፡፡
ሪፖርቱ እንዳመላከተው÷ ቡርኪና ፋሶ፣ ሄይቲ፣ ማሊ፣ የናይጄሪያ አንዳንድ ግዛቶች፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ለምግብ ዋስትና ችግር የሚጋለጡ ሀገራት ይሆናሉ፡፡
ከተጋላጭ ሀገራት መካከልም 75 በመቶውን የምትሸፍነው ሶማሊያ ልትሆን እንደምትችል ሪፖርቱ መጠቆሙን ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ተመድ፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ኤጀንሲዎች ለሪፖርቱ ዕውቅና ሰጥተው÷ ችግሩን በተቻለ መጠን ለመቅረፍ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
በሌላ በኩል በፈረንጆቹ 2022 በ58 ሀገራት እና ግዛቶች ወደ 258 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ለምግብ ዋስትና ችግር መጋለጣቸውን ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡
ይህም ከ2021 እና ከዚያ በፊት ካሉት ሰባት ዓመታት አንጻር በእጅጉ የከፋ መሆኑኑን ነው ሪፖርቱ ያመላከተው፡፡
በፈረንጆቹ 2021 ላይ 193 ሚሊየን ሰዎች በ53 ሀገራት እና ግዛቶች ለምግብ ዋስትና ችግር ተጋልጠው እንደነበርም ነው በሪፖርቱ የተጠቀሰው፡፡
በ2022 ሶማሊያ፣ አፍጋኒስታን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሄይቲ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ ሱዳን እና በየመን የሚገኙ ሰዎች÷ ለምግብ ዋስትና ችግር ተጋልጠው እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡
በወቅቱ 57 በመቶውን የሸፈነችውም ሶማሊያ እንደነበረች በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡