የሀገር ውስጥ ዜና

የጣሊያን ዳግም ወረራና የአርበኞች ተጋድሎ

By Shambel Mihret

May 04, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጣሊያን ኢትዮጵያን ዳግም የወረረችበትና ከጀግኖች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ጋር ለ5 አመት ታግላ የተሸነፈችበት 82ኛ አመት የድል በዓል ነገ ይከበራል፡፡

ጣሊያን በአድዋ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀል ዳግም ኢትዮጵያን የወረረችበትና ኢትዮጵያውያን አርበኞች ሕዝቡን በማስተባበር ከአምስት ዓመት ተጋድሎ በኋላ ጣሊያንን ሚያዝያ 27 ቀን 19 33 ዓ.ም ድጋሜ ድል አድርገዋል፡፡

የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ጣልያንን ያሸነፉበት የድል በዓል መታሰቢያ ሚያዝያ 27 ቀን 2015 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡

የአሁኑ ትውልድ የአርበኞችን የድል ታሪክ በተለያዩ ዘርፎች ውጤት በማስመዝገብ እንዲሁም የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ሊደግመው ይገባል ብለዋል፡፡

ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም የኢትዮጵያውያን የቁርጥ ቀን ልጆች የፋሽስት ጣሊያንን ወረራ የቋጩበት ቀን ነው፡፡

ከአድዋ ድል ማግስት ኢትዮጵያ የግዛት ማስፋፋት ልታስብ ትችላለች በሚል የብዙ ቅኝ ገዥ ሀገራትን ትኩረት ስባ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

በሰሜንና በደቡብ ምስራቅ ጣሊያን፣ በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ እንዲሁም በምስራቅ ፈረንሳይ እንደከበባ ያለ አካሄድ ቃጥቷቸው ነበር፡፡

የድንበር የውል ስምምነቶችን ወደ ጠረጴዛ ለማምጣት መሞከር ጣሊያን ለረጂም ጊዜ የሰራችው ኢትዮጵያን የመያዣና ለበቀል የሚሆን ጊዜ የማመቻቻ ስራዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡

ለዚህ አብነት የሚሆነው ጣሊያን በቅኝ በያዘቻት የያን ጊዜዋ የጣሊያን ሶማሌላንድና በኢትዮጵያ መንግስት በ1900 ዓ.ም የተደረገው ስምምነት ነው፡፡

ጣሊያን በአድዋ የገጠማትን ሽንፈት ቁስል በድል ለመሻር ሀገሪቱን ለመምራት ወደ ስልጣን የመጡት ሁሉ እያሰቡ እየተመኙ አመታት ቢያልፉም በ1922 ወደ ስልጣን የመጣው ሞሶሎኒ ተንኮል በመፈለግ እረፍት እንዳልነበረው ይጠቀሳል፡፡

በሐረር የኦጋዴን አውራጃ የወልወል ወረራም በዚሁ ስሜት የተወለደ መሆኑን ታሪክ ይነግረናል።

በሕዳር ወር 1927 ዓ.ም ለወልወል ግጭት በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መካከል በተደረገ የድንበር ስምምነት ስምምነቱን ለማስተግበር ወደ ስፍራው የሄዱ ኮሚሽነሮች ቦታው ላይ ሲደርሱ የጣሊያን ወታደሮች ቀድመው የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በማግኘታቸው ለቀናት በፍጥጫ ከቆዩ በኋላ ወደ ጦርነት አምርተዋል፡፡

ወልወል የኢትዮጵያ ይዞታ ብትሆንም በመንግስቱ የጥበቃ መዳከም ተጠቅማ የሰፈረችው ጣሊያን በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያ ላይ ተፅእኖ ማሳደሯን ቀጥላ እንደነበር ይታወቃል፡፡

የተፈጠረው መካረርም ወደ ጦር መማዘዝ እንዲያድግና የአድዋን የሽንፈት ካባ አውልቃ ኢትዮጵያን ድል ነስታ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያጣችውን ክብር ለመመለስ አጋጣሚውን እንደመንደርደሪያም ተጠቅማበታለች፡፡

ከሮም የተላከው የጣሊያን ጦር መስከረም 22 ቀን 1928 የመረብን ወንዝ ተሻግሮ በአድዋ፣ በአዲግራት ጦርነት ከፍቶ ነበር፡፡

ኢትዮጵያውያን አርበኞችና መሪዎችም ዓለም የጣሊያንን ወራሪነት እንዲያይና በከበባ ትጥቁን እንዲሁም ስንቁን ለማስጨረስ በማሰብ ጦሩ ምንም አይነት ችግር ሳይገጥመው ወደ መሀል ሀገር እንዲገባ ፈቀዱ፡፡

በ9 ክፍለ ጦሮች ተዘጋጅቶ ወደ ኢትዮጵያ የገባው የጣሊያን ጦር ቤታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ እርሻቸውን ሁሉ ትተው ጫካ በገቡ ኢትዮጵያውያን አርበኞች እረፍት እያጣም ቢሆን ለአምስት አመታት ቆይታ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያውያን የመንፈስና የአካል ጉዳት አቅም ሊያሳጣቸው ቢሞክርም ጠላትን እምቢ በማለት ዓድዋ ላይ ድል ያደረጉ አባቶችን ታሪክ በመድገም ከአምስት አመታት ትግል በኋላ ሀገራቸውን ከፋሽስት ነጻ አውጥተዋል፡፡

ጣሊያን 40 ዓመታት ያክል ስትዘጋጅ ቆይታ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ኢትዮጵያን የወረረች ቢሆንም የኢትዮጵያ አርበኞች በከፈሉት መስዋዕትነት በድጋሜ ድል ማድረግ ተችሏል፡፡

82ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች የድል መታሰቢያ በዓል ነገ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡

ቀኑ የኢትዮጵያ አርበኞች በአንድነት በፋሽስቱ ጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅት የከፈሉትን መስዋዕትነትና ያስገኙትን ድል ለማሰብ በየአመቱ ሚያዝያ 27 ቀን ይከበራል፡፡

በየሻምበል ምሕረት