የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ክልል ከግንቦት ወር ጀምሮ የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ብቻ እንደሚካሄድ ተገለፀ

By Mikias Ayele

May 07, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት  ብቻ እንደሚካሄድ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ማሄ ቦዳ  እንደገለጹት÷ የነዳጅ ግብይት በዲጅታል የክፍያ ስርዓት እንዲከናወን እንደአገር በተያዘው አቅጣጫ መሰረት በደቡብ ክልል ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ሲደርግ ቆይቷል።

አሽከርካሪዎች እና የነዳጅ ማደያ የሽያጭ ሠራተኞች ከዲጅታል ግብይት ስርአቱ ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግም ከሚያዝያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የነዳጅ ግብይቱ በሙከራ ደረጃ በቴሌ ብር ክፍያ መደረጉን ጠቁመዋል።

በዚህም ከመጪው ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ በሚገኙ 136 የነዳጅ ማደያዎች ግብይቱ ሙሉ ለሙሉ በቴሌ ብር ብቻ እንደሚሆንም አስታውቀዋል።

ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ነዳጅን ከዲጂታል የክፍያ ስርአት ውጭ እጅ በእጅ በገንዘብ ሲሸጡ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡