የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ልማት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

By Feven Bishaw

May 11, 2023

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ልማት ስትራቴጂ ይፋ ሆኗል፡፡

በበስትራቴጂ ይፋ ማድረጊያ መርሐ ግብሩ÷ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ሚኒስትሮች እና የልማት አጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል።

ስትራቴጂው እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር እስከ 2050 ድረስ የሚተገበር እና በፈረንጆቹ 2015 ከጸደቀው የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ጋር የተጣጣመ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት ያዘጋጀው ይህ የልማት ስትራቴጂ በ2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ ታላሚ ያደረገ ስለመሆኑም ተጠቁሟል።

ስትራቴጂው ከፓሪሱ ስምምነት በተጨማሪ ከሀገሪቱ የአስር ዓመት የልማት ዕቅድና ሌሎች የረጅም ጊዜ የልማት ግቦች ጋር የተጣጣመ ነውም ተብሏል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረጓን ገልጸዋል።

ከ200 በላይ የአየር ንብረት ለውጥ ማገገሚያ ፕሮጀክቶች ገቢራዊ መሆናቸውን መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ልማት ስትራቴጂ በተሟላ መልኩ ገቢራዊ ሲሆን÷ እስከ 2050 የሀገሪቱን አጠቃላይ ምርት ዕድገት አሁን ካለው አንፃር 66 በመቶ ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በስትራቴጂው ትግበራ የማይበገር የግብርና ልማትን በማፋጠን እስከ 2050 ድረስ 20 ሚሊየን ቶን ምርት ከአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በመታደግ ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ተይዟል።