የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል 126 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ባለሐብትነት ተሸጋገሩ

By Meseret Awoke

May 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል 126 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ባለሐብትነት ማሸጋገሩን የክልሉ ሥራና ሥልጠና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ያዘጋጀው 8ኛ ዙር የክኅሎት፣ የቴክኖሎጂና የተግባር ተኮር ጥናትና ምርምር የውድድር መድረክ በደብረ ብርሀን ከተማ እየተካሄደ ነው።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አረጋ ከበደ እንዳሉት ፥ ኢንተርፕራይዞቹ በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ናቸው።

ሥራና ሥልጠና ቢሮው ወደ ባለሐብትነት የተሸጋገሩትን ኢንተርፕራይዞች ለክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨትመንት ቢሮ አስረክቧል።

የተሸጋገሩት ኢንተርፕራይዞች የቦታና የብድር አቅርቦት እንደሚመቻችላቸውም ጠይቀዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ደኤታ ንጉሱ ጥላሁን ፥ ኢንተርፕራይዞችን ማሸጋገር ብቻ በቂ አይደለም ብለዋል፡፡

በዚህም የመሥሪያ ቦታ እና ካፒታል ማሟላት ከመንግስት እንደሚጠበቅ ጠቁመው ፥ ለአምራቾቹ የገበያ ትሥሥር መፍጠር ሌላው የመንግስት ድርሻ መሆኑንም ተናግረዋል።

መድረኩ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ዛሬን ጨምሮ ለአራት ቀናት ይቆያል፡፡

በአላዩ ገረመው