የሀገር ውስጥ ዜና

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 20 ሚሊየን ወጣቶች እንደሚሳተፉ ተገለጸ

By Amele Demsew

May 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ 20 ሚሊየን ወጣቶችን በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማሳተፍ ዝግጅት መጠናቀቁን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ እንደገለጹት፥ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተደራሽነት አድማሱን በማስፋት 20 ሚሊየን ወጣቶች እንዲሳተፉ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በጎ ፈቃደኞቹ በ13 የሥምሪት መስኮች እንደሚሰማሩና በዚህም 51 ሚሊየን የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ነው የተናገሩት።

የአረንጓዴ አሻራ፣ ደም ልገሳ፣ የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች የቤት እድሳት፣ የትራፊክና የመንገድ ደኅንነት አገልግሎትና የማጠናከሪያ ትምህርት ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተለያዩ የሙያ ዘርፎችን ያካተተው የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም እንደሚካተት ተገልጿል።

”በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ ሁለት” በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው የዘንድሮው በጎ ፈቃድ አገልግሎት አምና ተሳታፊ ያልነበሩት የትግራይ ክልል ወጣቶችም ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፍ የሚፈልጉ ወጣቶች በየአካባቢያቸው የተዘጋጁላቸውን አማራጮች በመጠቀም ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩጥሪ መቅረቡን ኢዜአ ዘገቧል።