የሀገር ውስጥ ዜና

የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተና መሆኑን በመለየት በትኩረት ለመስራት አቅጣጫ ተይዟል -ፕላንና ልማት ሚኒስቴር

By Shambel Mihret

May 17, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተና መሆኑን በመለየት በትኩረት ለመስራት አቅጣጫ መያዙን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው 19ኛ መደበኛ ስብሰባ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የተቋማቸውን  የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ በማክሮ ኢኮኖሚና ሌሎች ሀገራዊ የልማት ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራትን አብራርተዋል።

የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ በተተገበረባቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ያጋጠሙ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎችን በመቋቋም የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት በማደግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በ2015 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት አመላካች ውጤቶች መኖራቸውንም ነው የጠቀሱት፡፡

በማምረቻው ዘርፍ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተከናወኑ ተግባራት፣ በአገልግሎት ዘርፍ የታየው መነቃቃት እቅዱን ለማሳካት ያግዛልም ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተና መሆኑን በመለየት በትኩረት ለመስራት አቅጣጫ መያዙን ገልጸዋል።

ሪፖርቱ በተገመገመበት ወቅት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የልማት ዕቅድን እንደ ሀገር ወጥ ለማድረግ አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስቧል፡፡