የሀገር ውስጥ ዜና

ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢኮኖሚው  6 ነጥብ 2 በመቶ አድጓል- ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)

By Mikias Ayele

May 20, 2023

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተተገበረው የመጀመሪያው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፈተናዎችን ተቋቁሞ በአማካይ 6 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ  ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ።

የ2015 በጀት ዓመት የመንግስት የዘጠኝ ወራትና የሦስተኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ሚኒስትሮች በተገኙበት ተካሂዷል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ  ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)በዚሁ ወቅት÷ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የመጀመሪያ ምዕራፍ አፈጻጸምና የሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ዝግጅትን  በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

መንግስት ከ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተቀዳውን የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ሦስት ዓመታት በመተግበር ስኬት ማስመዝገቡን አንስተዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተፈጥራዊ እና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች ውስጥም ሆኖ ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ካስመዘገቡት አማካኝ የ3 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ሲነጻጸር በእጥፍ ማደጉን ገልጸዋል።

መንግስት በወሰዳቸው ቁልፍ እርምጃዎችና የራስን አቅም አሟጦ መጠቀም ላይ ባተኮሩ ተግባራት ኢኮኖሚው ባለፉት ሦስት ዓመታት በአማካይ የ6 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ መጠናቀቁን ተከትሎም  ከ2016 እስከ 2018 የሚተገበር ሁለተኛ ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ መዘጋጀቱን ሚኒስትሯ  መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህኛው ምዕራፍ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን መገንባት፣ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ አካባቢ መፍጠር፣ የዘርፎችን የማምረት አቅምና ምርታማነት ማስፋት እና የመንግስትን የመፈጸም አቅም ማጎልበት ላይ ያተኮሩ አራት ቁልፍ ምሰሶዎች መለየታቸውን ገልጸዋል።

ለሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምዕራፍ ስኬት በልማት ፋይናንስ፣ በኢንቨስትመንት፣ በገበያ ማስፋት፣ ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር እና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ዙሪያ ቅንጅታዊ አሰራርን መከተል እንደሚገባ አስረድተዋል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የተያዘው ሀገራዊ ግብ እንዲሳካ ቁልፍ ሚና ያለው ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ ቀዳሚው ስራ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።