የሀገር ውስጥ ዜና

የማህበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት ቴሌቪዥን ፈቃድ በጊዜያዊነት ታገደ

By Meseret Awoke

May 21, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የማህበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት ቴሌቪዥን ፈቃድ በጊዜያዊነት መታገዱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር አንቀፅ 70 ከተጠቀሱት ውስጥ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን በሐይማኖት ተከታዮች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት ማነሳሳት ወይም በሐይማኖት ተከታዮች መካከል አለመቻቻል እንዲፈጠር መቀስቀስ የሌለባቸው መሆኑ መደንገጉን ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡

ይሁንና ማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ በግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም ሰበር ዜና በሚል ባሰራጨው መግለጫ ከሐይማኖት መገናኛ ብዙኃን ሚና ውጪ በሆነ አግባብ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያካሄደውን ስብሰባ የሚያውክና ህዝብን ለግጭት የሚያነሳሳ መልዕክት ማሰራጨቱ ተረጋግጧልም ነው ያለው፡፡

ይህም የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን የሚተላለፍና በሀገር ሁለንተናዊ ሰላም ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል እንደሆነም አብራርቷል፡፡

በመሆኑም ከጉዳዩ አጣዳፊነትና ሊያስከትለው ከሚችለው ጉዳት አንፃር በቀጣይ በባለሥልጣኑ ቦርድ ታይቶ ዘላቂ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ የጣቢያው ፈቃድ በጊዜያዊነት የታገደ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!