አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሕብረት 60ኛ ዓመት ምስረታን አስመልክቶ የተዘጋጀው “ዋን አፍሪካ ኤክስፖ” ዛሬ በሳይንስ ሙዚየም ተከፍቷል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው ኤክስፖ ÷የመንግስትና የግል የንግድ ዘርፎች፣ የአፍሪካ ፣ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እና ነጋዴዎች ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን እንደሚያስተዋውቁበት ተገልጿል።
ኤክስፖው እስከ ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን÷በአፍሪካ ኩባንያዎች መካከል የንግድ ትስስርን ለማሳለጥ እድል እንደሚፈጥር ተመላክቷል።
በኤክስፖው መክፈቻ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር አብዲ ያሲን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌና ከተለያዩ ሀገራት የተወጣጡ እንግዶች ተገኝተዋል።
የቱሪዝም፣ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች እና መሰረተ ልማቶችን የተመለከቱ ተሞክሮዎች በኤክስፖው እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል፡፡
ይህም ለአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ ትስስርና እድገት የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡