የሀገር ውስጥ ዜና

በሚያለያዩን ጉዳዮች ላይ በመመካከር ለችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ መሻት ይጠበቅብናል – መስፍን አርዓያ ፕ/ር

By Tamrat Bishaw

May 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለተውጣጡ ዜጎች ስልጠና እየሰጠ ነው።

በመድረኩ የተገኙት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ÷ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሚያደርጉት ሀገራዊ ምክክር ልዩነት የፈጠሩ ጉዳዮች ተለይተው ምክክር ይደረግባቸዋል ብለዋል፡፡

ችግሮቻችን በሙሉ በመወያየት የሚፈቱ ናቸው ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ÷ ኢትዮጵያውያን በሰከነ ሁኔታ ሊወያዩ ይገባል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአሁኑ ወቅት ከምንም በላይ የሚያስፈልጋቸው ሰላም መሆኑን ጠቁመው÷ ከግጭት አዙሪት ለመውጣትም ምክክር የግድ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በፖለቲካ ልሂቃን መካከል ውይይቶች መካሄዳቸውን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ÷ ህብረተሰቡን ያሳተፉ ባለመሆናቸው ውጤታማ ነበሩ ለማለት አያስደፍርም ነው ያሉት።

በሀገራዊ ምክክሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ሴቶችና ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የሃይማኖትና የባህላዊ መሪዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ መንግስትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

በአለማየሁ መቃሳ