አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከግንቦት 11 እስከ 17 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል ከ161 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ 92 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 68 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የወጪ በድምሩ ከ161 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል ብሏል፡፡
ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች ፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገራ ገንዘቦች ይገኙበታል ነው የተባለው፡፡
በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የወጪ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር አዋሽ፣ ጅግጅጋ እና ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የላቀ አፈጻጸም አስመዝግበዋል።
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙናቸው ነው የተባለው፡፡
የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ አምስት ግለሰቦች እና ስድስት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታት ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።