አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመካላከያ ሚኒስቴር ዋር ኮሌጅ ከፍተኛ አመራሮች እና ሰልጣኝ መኮንኖች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጎበኙ።
የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ሰልጣኞች የሚሰጠውን የንድፈ ሐሳብ ትምህርት ጨርሰው የተግባር ምልከታ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አድርገዋል፡፡
ሰልጣኝ የጦር መኮንኖች በዓለም አቀፍ ጉዳዮች እና በሀገራዊ የደኅንነት ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ የአመራር እና የሌሎች ወታደራዊ ዘርፎች በተግባር የተደገፈ ዕውቀት ቀስመዋል።
የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽኅፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ÷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና መከላከያ ሰራዊት በአፈጣጠራቸው ተመሳሳይነት ያላቸው መሆናቸውን ገልፀዋል።
የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ቡልቲ ታደሰ በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያን ገፅታ በበጎ ሁኔታ እንዲነሳ ያደረጉ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች በሚገኙበት ተቋም በመገኘት ለሰልጣኝ መኮንኖች ለተሰጠው ገለፃ ምሥጋና አቅርበዋል።
የሀገር መከላከያ ዋር ኮሌጅ በሰው ኃይል ግንባታ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር እና ሥልጠናዎችን በመስጠት በሰው ኃይል ግንባታ ብቁ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ሰራዊቱ በዓለም ሠላም ማስከበር እና በሌሎች ተልዕኮዎች ውጤታማነቱን ማስመስከሩንም አስታውሰዋል፡፡
ዋር ኮሌጁ በቀጣይ የተሻለ ተግባር እንዲከውን የሚያስችል ሥልጠና እየሰጠ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በጉብኝቱ ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲቲዩት የፖለቲካ ሳይንስ መሪ ተመራማሪ የሆኑት ዳር እስከዳር ታዬ (ዶ/ር) “የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ትናንት እና ዛሬ” በሚል የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል።
በውይይቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ጎብኚዎች በቀረበው ጽሑፍ ላይ ጥያቄ እና አስተያየት ሰጥተዋል።