አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመኖሪያ ቤትና ለተለያዩ የልማት ተግባራት የሚውሉ ቦታዎች ላይ ሲያከናውን የነበረው የጨረታ ሰነድ ሽያጭ ተጠናቅቆ በይፋ ተከፍቷል።
ጨረታው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ቀነአ ያደታ (ዶ/ር) በተገኙበት ነው በዛሬው ዕለት የተከፈተው፡፡
በቢሮው መሬትን በሊዝ ለጨረታ የማቅረብ ሒደት ለአምስት ዓመታት ያክል ተቋርጦ እንደነበር ሃላፊው አስታውሰዋል፡፡
መሬት በግልጽነት ለዜጎች እንዲተላለፍ ዝግጀት ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመው÷ በቀጣይ አጠር ባለ የጊዜ ገደብ የሊዝ ጨረታው እንደሚካሄድ መግለጻቸውን የከተማዋ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል።
በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት ቢሮ የለማ መሬት ማስተላለፍና ሊዝ ክትትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጥላሁን በበኩላቸው÷በ10 ቀናት 24 ሺህ ሰነድ ለሽያጭ ቀርቦ 21 ሺህ 600 መሸጡን ተናግረዋል፡፡