የሀገር ውስጥ ዜና

ሀገር አቀፍ የሥነ-ምግባርና የሙስና መከላከል ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጀ

By Amele Demsew

June 01, 2023

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገር አቀፍ የሥነ-ምግባርና የሙስና መከላከል ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱን የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ ፖሊሲውን በሚመለከትና አሰራሩን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ እየሰራ ያለውን ሥራ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።

የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ የሙስና ወንጀል በዜጎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ እያደረሰ ያለው ጫና ማኅበራዊ ቀውስ እያስከተለ ከመሆኑ ባሻገር ሀገራዊ ሥጋት ሆኗል ፡፡

በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ የጸረ ሙስና ትግሉን ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችል ሀገር አቀፍ የሥነ-ምግባርና የሙስና መከላከል ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ረቂቅ ፖሊሲው በጥናት ላይ የተመሰረተና የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ከግምት ያስገባ እንዲሁም የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ረቂቅ ፖሊሲ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ፖሊሲውን በሚመለከት የክልልና የከተማ መስተዳድር ተጠሪ ተቋማት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

ከዚህ ጎን ለጎን በውይይቱ በሙስና ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራትን በቴክኖሎጂ አሰራር ለመደገፍ የተከናወኑ ተግባራትም ውይይት እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ውይይቱ ዛሬን ጨመሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡