አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 4ኛው “ብሩህ ኢትዮጵያ” ሀገር አቀፍ የሥራ ፈጠራ ውድድር ከፊታችን ግንቦት 28 ቀን ጀምሮ እንደሚካሄድ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ውድድሩ ከግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለ15 ቀናት በቡራዩ ተሰጥኦ ማበልጸጊያ ማዕከል እንደሚካሄድ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡
መርሐ ግበሩ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች በየደረጃው በማወዳዳር ሀሳባቸው የሥራ ዕድል እንዲፈጥር የማድረግ ዓላማ ያለው ነው ብለዋል።
በዘንድሮው ውድድር በ1 ሺህ 240 ያህል ወረዳዎች፣ በ98 ዞኖች፣ በ50 ዩኒቨርሲቲዎች የውድድር መስፈርት ተዘጋጅቶ መሰጠቱን ገልፀዋል።
በዚህም ከአፋርና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ውጪ በ10 ክልሎች በየደረጃው ውድድር እንዲካሄድ መደረጉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በ4ኛው “ብሩህ ኢትዮጵያ” ሀገር አቀፍ የሥራ ፈጠራ ውድድር 200 ሀሳቦች በተለያዩ ደረጃዎች ቀርበው የሚወዳደሩ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ከእነዚህም 70 የሚሆኑት ሀሳቦች ተለይተው የመጨረሻዎቹን 50 ምርጥ ሀሳቦች የሥራ መነሻ ካፒታል ለእያንዳንዳቸው 5 ሺህ ዶላር ሽልማት ይበረከትላቸዋል ተብሏል።