የሀገር ውስጥ ዜና

ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን ከ7 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተዘጋጁ

By Meseret Awoke

June 03, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን ከ7 ቢሊየን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሞቱማ ቶሌራ(ዶ/ር) ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት ከአራት ዓመት በፊት በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ25 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከል ችላለች፡፡

የሀገሪቱን ምርታማነት ለማሳደግ፣ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የደን ሽፋኑን በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ታላሚ ባደረገው በዚህ መርሐ ግብር ከተተከለው አጠቃላይ ችግኝ 55 በመቶ የሚሆነው ለጥምር ደን መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሞቱማ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት ፥ ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተከናወነው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉ በስኬቱና ህዝባዊ ተሳትፎን በማረጋገጥ የሚጠቀስ ፕሮጀክት ነው፡፡

“በኢትዮጵያ በየዓመቱ በብዙ ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ካልተተከሉ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለከፋ አደጋ የምንጋለጥበት ዘመን በመሆኑ ለኢትዮጵያውያን ችግኝ መትከል የምርጫ ጉዳይ አይደለም” ብለዋል፡፡

ተራራማ አካባቢዎች እየተራቆቱ፣ አፈር እየተሸረሸረ፣ የውኃማ አካላት እየደረቁ፣ መምጣታቸውን ጥናቶች እንደሚያሳዩ ጠቁመው ፥ አረንጓዴ አሻራ ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ6 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ቢያዝም እስካሁን ከ7 ቢሊየን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ ምን ዓይነት ችግኞች በምን አይነት ሥነ ምህዳርና በምን አይነት አፈር ላይ ይተከሉ የሚለው በጥናት ተለይቶ ለተከላ ዝግጅት መደረጉን በማብራራት፡፡

በዚሁ መሰረት እስካሁን ከ902 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ተለይቶ ለችግኝ መትከያ የተዘጋጀ ሲሆን ፥ ከዚህ ውስጥ 522 ሺህ ሄክታር የሚሆነው ለደን መለየቱን ጠቁመዋል፡፡

ለችግኝ መትከያ ከተለየው መሬት ውስጥ 257 ሺህ ሄክታር የሚሆነው ካርታ እንደተዘጋጀለት ነው የገለጹት፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ በተካሄዱት አራት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች ከዘር መረጣ ጀምሮ በችግኝ ተከላና በእንክብካቤ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አረጋግጠናል ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አካል በሆነው የበጋ ወቅት የተቀናጀ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ የዜጎች ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ ለዚህ ማሳያ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

ችግኝ መትከል የመርሐ ግብሩ የመጀመሪያ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው ፥ የተተከሉ ችግኞች ለሚፈለገው ዓላማ ውለው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ የመጨረሻ ግቡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዘንድሮው መርሐ ግብር እስካሁን ወደ 2 ነጥብ 3 ቢሊየን የሚጠጋ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በ2015 የበልግ ወቅት በኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ድሬዳዋ ከ 250 ሚሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውንም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያነሱት፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች በደን ልማት፣ በምግብ ዋስትና፣ በአፈር ለምነትና መሰል ጉዳዮች ላይ ያመጡትን አዎንታዊ ለውጥ አጥንቶ ይፋ የሚያደርግ ድርጅት መለየቱንም ጠቁመዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!