የሀገር ውስጥ ዜና

የፓን አፍሪካ ፓርላማ መደበኛ ስብሰባ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቀቀ

By Alemayehu Geremew

June 05, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 6ኛው የፓን አፍሪካ ፓርላማ 2ኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቀቀ፡፡

በጉባዔው ማጠቃለያ ላይ ከየሀገራቱ የተውጣጡት የፓርላማ አባላት ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

6ኛው የፓን አፍሪካ ፓርላማ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ “የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ትግበራን ማፋጠን እና በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲ ላይ” ያተኮረ ነበር፡፡

ጉባዔው ከግንቦት 8 እስከ 25 / 2015 ዓ.ም ላለፉት ሁለት ሳምንታት በደቡብ አፍሪካ ሚድራንድ ተካሂዷል።

በስብሰባው በርካታ የአኅጉሩ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ ፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

በተጨማሪም የሠላምና የፀጥታ ጉዳዮች እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳዎች ውይይት ተካሂዶባቸው በርካታ ምክረ-ሐሳቦችና ውሳኔዎች የተላለፉበት እንደነበረ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የፓርላማ አባላቱ ከየሀገሮቻቸው መንግሥታት ጋር በመመካከር የጋራ ሥምምነቶችን እንዲያጸድቁ የሚያስችላቸውን ሥራ እንዲያከናውኑ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

ለአብነትም በዓለም አቀፍ ወንጀሎች ፣ በዓለም አቀፍ ኅጎች እና ስለሚዳኙበት ሁኔታ ዓላማ አድርጎ በተቀረጸው የአፍሪካ ፍርድ ቤት እንዲሁም የአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ለማቋቋም የተዘጋጀውን የማላቦ ሥምምነት እንዲፈርሙና እንዲያፀድቁ የሚያስችላቸውን ሥራ ያከናውናሉ ተብሏል፡፡

በሌላ በኩልም ስብሰባው ከዚህ ቀደም ወጥተው በነበሩ ሕጎች ላይ በመወያየት የተለያዩ ማሻሻያዎችን ያደረገ ሲሆን ፥ አዳዲስ የተዘጋጁ የሕግ ረቂቆችንም አፅድቋል፡፡

በተጨማሪም የተለየዩ የፓርላማው ኮሚቴዎች አዳዲስ አኅጉራዊ ሕግ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ረቂቅ ሕጎችን በማዘጋጀት ለሚቀጥለው 3ኛ መደበኛ ስብሰባ እንዲቀርቡ ውሳኔዎችንም አስተላልፏል፡፡

አባል ሀገራቱ በየፓርላማዎቻቸውና በየሀገሮቻቸው የፓን አፍሪካ ፓርላማና ዓላማዎቹን በማስተዋወቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ተወስኗል፡፡

በጉባዔው ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶን ጨምሮ ሦስት የምክር ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።