አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩ 28 ግለሰቦች ላይ የ14 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ለዐቃቤ ሕግ ፈቅዷል፡፡
ፍድር ቤቱ በዐቃቤ ሕግና በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል የተነሳውን መከራከሪያ ነጥብ ከመረመረ በኋላ ነው ክስ የመመስረቻ ጊዜ የፈቀደው።
የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ በነ መላክ ምሳሌ እና በነ ደበበ በሻህ ውረድ መዝገብ የተካተቱ አጠቃላይ 28 ተጠርጣሪዎች ላይ ሲያከናውን የቆየውን ምርመራ ማጠናቀቁን አስታውቋል።
በመዝገቡ ላይ የተሰየመው የተደራጁና የፀረሽብር ወንጀል ጉዳዮች ዳሪክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም ከፖሊስ የምርመራ መዝገቡን መረከቡን ገልጿል።
በዚህም በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል 1ሺህ 280 ሰነዶች በመዝቡ ላይ መኖሩን የጠቀሰው ዐቃቤ ሕግ ሰነዶችን ተመልክቶ ለመወሰንና ክስ ለመመስረት የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው÷ በተለያዩ እስር ቤቶች ተጠርጣሪዎቹ ለ43 ቀናት ምርመራ ሲከናወንባቸው መቆየታቸውን በመጥቀስ ተጨማሪ ጊዜ በስር መቆየት የለባቸውም ሲሉ ተከራክረዋል።
በተጨማሪም ዐቃቢቤ ሕግ ባቀረበው ክስ የመመስረቻ አቤቱታው ላይ ተጠርጣሪዎቹ ዋስትና ሊያስከለክላቸው የሚያስችሉ ፍሬ ነገሮች አልተጠቀሱም በማለት የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ጠበቆቹ በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 109 ድንጋጌ ላይ የክስ መመስረቻ እንጂ የተጠርጣሪዎችን አቆያየት የሚመለከት ድንጋጌ የለም ሲሉ ተከራክረዋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የተጠርጣሪዎችን አቆያየትን በሚመለከት ተገቢውን ትዕዛዝ የሚሰጠው ፍርድ ቤቱ መሆኑን አብራርቷል።
በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን ምርመራእንደሚመራ የገለጸው ዐቃቤ ሕግ ምርመራን ቢመራም የተሰበሰቡ ሰነዶችን ሁሉ ማወቅ እንደማይችል ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ መልስ ሰጥቷል።
አቆያየታቸውን በሚመለከት ክስ እስክንመሰርት በማረፊያ ቤት ይቆዩ እና በመደበኛው ችሎት ክስ ስንመሰርት በዋስትና ላይ ክርክር ይደረግ ነው ያልኩት ሲል መልስ ሰጥቷል።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው÷ አጋጥሞናል ባሉት የጤና ዕክልን በሚመለከት በፌዴራል ፖሊስ በኩል ህክምና ያገኙ መሆናቸው የጠቀሱ ቢሆንም የህክምና ውጤቱን በሚመለከት ግን ወደ ህክምና ተቋም በወሰዱን ፖሊስ በኩል ውጤታችንን እንዳናውቅ ተደርገናል በማለት አቤቱታ አቅርበዋል።
መዝገቡን የተመለከቱት ዳኛ በኩል በችሎት የተገኘው መርማሪ ፖሊስ ስለጉዳዩ መልስ እንዲሰጥ የተጠየቀ ቢሆንም መርማሪው ስለጉዳዩ በግሉ እንደማያውቅ በመጥቀስ ወደ ህክምና ለወሰዳቸው መርማሪ ትዛዝ ይሰጥ ሲል መልስ መስጠቱን ተከትሎ እንደግለሰብ ሳይሆን እንደተቋም መልስ መሰጠት እንዳለበት ተጠቅሶ በችሎቱ ዳኛ ለፖሊስ ግንዛቤ ተሰጥቷል።
በተጨማሪም ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ በገላን አካባቢ በእስር ቤት ውስጥ ደርሶብናል ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጠቅሰው በጽሁፍ እንዲያቀርቡ በታዘዙት መሰረት ተጠርጣሪዎቹ በጽሁፍ ለችሎቱ አቅርበዋል።
እንዳጠቃላይ ክርክሩን የተከታተለው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ በግራ ቀኝ የተነሳውን ክርክር መርምሮ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና መብት ውድቅ በማድረግ ለዐቃቤ ሕግ ክስ የመመስረቻ ጊዜ መስጠት እንደሚገባ በማመን ከጠየቀው 15 ቀን ውስጥ የ14 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።
ፍርድ ቤቱ በቁጥጥር ስር ስንውል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞብናል ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምርመራ አድርጎ ውጤቱን እንዲያቀርብ አዝዟልል።
በሌላ በኩል መርማሪ ፖሊስ በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ አካባቢ በመከላከያ ላይ ውጊያ ከፍተው በተደረገ ሕግ ማስከበር ስራ በቁጥጥር ውለዋል ባላቸው በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ በ 10 ግለሰቦች ላይም ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ክርክር ተደርጎበታል።
ከዚህ በፊት በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ወስጥ ተጠርጣሪዎችን ቃል የመቀበልና እና አሻራ የማስነሳት ስራ መስራቱን ገልጿል።
ቀረኝ ያላቸው ማለትም ግብረዓበር ተከታትሎ መያዝ፣ የቴክኒክ ማስረጃ ማስመጣት፣ ተጠርጣሪዎቹን የነፍስ ወከፍና የቡድን መሳሪያ ይዞ ኢግዝቪት የማድረግ ስራ እና ቀሪ ማስረጃ መሰብሰብ እንደሚቀሩት ጠቅሶ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል።
በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል ተጠርጣሪዎች እርሻ ውስጥ እንጂ ውጊያ ከፍተው አይደለም የተያዙት የሚል መከራከሪያ ነጥብ አንስተው ነበር።
በተጨማሪም ጦርነት ከፍተው ከተባለ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሽብርተኛ ተብሎ ባልተፈረጀበት ሁኔታ ላይ ጦርነት ከፍተው መባሉ አግባብ አደለም በማለት የፖሊስን የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄን ተቃውመው ተከራክረዋል።
በተጨማሪም አንድ ተጠርጣሪ ላይ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ደርሶበታል ሲሉም ጠበቆቹ አቤቱታ አቅርበዋል።
ክርክሩን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ መርምሮ ከወንጀሉ ልዩ ባህሪና ውስብስብነት አንጻር ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው በማለት የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
ይህ በእንዲህ እያለ ፍርድ ቤቱ አራት ተጠርጣሪዎች ማለትም ዶ/ር በቀለ ኃይሌ፣ ጌታቸው ጥዑምሌሳን፣ ሙሉቀን ወንዴና ጌትነት ወንዶሰን የተባሉ ግለሰቦች ላይ ፖሊስ ዋስትና መብታቸው ቢጠበቅ እንደማይቃወም ባቀረበው ጥያቄ መነሻ በማድረግ ከ10 ሺህ ብር እስከ 2 ሺህ ብር የሚደርስ ዋስ አስይዘው ከስር እንዲፈቱ አዝዟል።
በታሪክ አዱኛ