የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ ከተማ ፣ የኦሮሚያ እና የአፋር ክልል አመራሮች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው

By Shambel Mihret

June 13, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ፣ የኦሮሚያ እና የአፋር ክልል የአመራሮች የውይይት መድረክ መካሄድ ጀመረ፡፡

መድረኮቹ የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባስቀመጠው አቅጣጫ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አመራሮች እያካሄዱት ባለው ውይይት ላይ እንደተገለጸው÷ ውይይቱ ዓለም አቀፋዊ፣ ቀጣናዊና ሀገራዊ ጉዳዮች በስፋት የሚዳሰሱበት ነው፡፡

እንዲሁም ስኬቶችና ተግዳሮቶችን ተገንዝቦ ስኬትን ለማላቅ ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል ለመቀየር ስንቅ ለመያዝ እና የላቀ ዝግጁነትን ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል፡፡

ውይይቱ ለአራት ቀናት ይቆያል መባሉን የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል አመራሮች ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በውይይቱ ከ2 ሺህ 58 በላይ አመራሮች እየተሳተፉ መሆኑን ኦቢኤን ዘግቧል፡፡

የዓለምን ወቅታዊ ሁኔታ እና የሀገሪቱን ችግሮች ለመፍታት አዳዲስ ሐሳቦችን በማንሳት መሥራት የመሪዎች ኃላፊነት ስለመሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡

ውይይቱ ለሶስት ቀናት ይቀጥላል ነው የተባለው፡፡

በተመሳሳይ የአፋር ክልል ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮችን ያሳተፈ የወል እውነት፣ ፈጠራና ፍጥነት በሚል ነጥቦች ላይ የሚያጠነጥን የውይይት መድረክ በሰመራ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል ደስታ ሌዳሞ እንደገለጹት ፥ ብልጽግና ፖርቲ ከዚህ በፊት በሀገር ጉዳይ እኩል የመሳተፍና የመወሰን ጥያቄዎች በአግባቡ በመመለስ እውነተኛ ህብረ-ብሄራዊ ፌደራሊዝም በመተግበር ላይ ይገኛል።

“እንደሀገርና ህዝብ ያላለፍናቸዉ ቀሪ ፈተናዎችን ያሉብን በመሆኑ ኢትዮጵያዉያን ተባብረንና ተደጋግፈን በጋራ መቆም ይጠበቅብናልም” ነው ያሉት።

ከዚህ አንጻር በየደረጃዉ የሚገኙ የፖርቲዉ አመራሮች ተጨባጭ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በአግባቡ ተረድቶ ተገቢዉን ግብረ-መልስ መስጠት ይጠበቅበታል ማለታቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።