አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የዋና ጸሐፊው ወርቅነህ ገበየሁን (ዶ/ር) የሥራ ዘመን ለተጨማሪ አራት ዓመታት አራዘመ።
በተጨማሪም አባል ሀገራት በዙር በሚደርሳቸው የሊቀመንበርነት ኃላፊነት ስልጣን ላይ ለውጥ መደረጉን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህም ላለፉት አራት ዓመታት ኢጋድን በሊቀመንበርነት ስትመራ የቆየችው ሱዳን ለጅቡቲ ኃላፊነቱን አስረክባለች።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ኢጋድን ለዘጠኝ ዓመታት በሊቀመንበርነት መምራቷ ይታወሳል።
በጅቡቲ በተካሄደው የኢጋድ የመሪዎች ጉባዔ ላይ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንቶች ተሳትፈዋል።
ጉባዔው በሱዳን እና ሶማሊያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡