የሀገር ውስጥ ዜና

በ50 ሚሊየን ዶላር ወጪ የተገነባው የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል ተመረቀ

By Feven Bishaw

June 13, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በ50 ሚሊየን ዶላር ወጪ የተገነባው የዊንጉ አፍሪካ የግል ዳታ ማዕከል ተመርቋል።

ዛሬ በአዲስ አበባ በተካሄደ የምረቃ ስነ- ስርዓት ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት እና የዊንጉ አፍሪካ የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የዊንጉ አፍሪካ ዋና ስራ አስፈፃሚ አንቶኒ ቮስካሪደስ እንዳሉት÷ ዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል ለማንኛውም የመንግስትና የግል ተቋም በተመጣጣኝ ዋጋና ደህንነቱ የተጠበቀ የመረጃ አገልግሎት የሚሰጥ ነው።

ዊንጉ አፍሪካ ሁሉንም አይነት ቴክኖሎጂዎች የሚጠቀም፤ በሶማሊ ላንድ፣ ጅቡቲና ታንዛኒያ አገልግሎት የሚሰጥ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ቋት መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጥና ወጪ ቆጣቢ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት መሆኑን ጠቁመዋል።

የዊንጉ አፍሪካ ቺፍ ስትራቴጂ ኦፊሰር ኒኮላስ ሎጂ÷ በ50 ሚሊየን ዶላር የተገነባው ማዕከሉ የኢትዮ ቴሌኮም፣ ሳፋሪ ኮም ኢንተርኔት ማዕከል በጋራ የሚጠቀም ፈጣንና አስተማማኝ የመረጃ ማዕከል እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው የውጭ ባለሀብቶች ደህንነቱ የተጠበቀ አማራጭ የመረጃ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።