አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ከኔዘርላንድስ ንግድ እና የልማት ትብብር ሚኒስትር ሊሴይ ሼሪንማሸር ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸው ሚኒስትር ዴኤታዋ ኢትዮጵያ እና ኔዘርላንድስ ያላቸውን አጋርነት አንስተው፥ የኔዘርላንድስ መንግስት በዘርፈ ብዙ ተቋማት እና በግሉ ዘርፍ ለኢትዮጵያ እያደረገ ስላለው የልማት ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የልማት ትብብር ለማሳደግ በትብብር እንደሚሰራም አብራርተዋል።
የኔዘርላንድስ ንግድ እና የልማት ትብብር ሚኒስትር ሊሴይ ሼሪንማሸር በበኩላቸው ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ አድንቀው ኔዘርላንድስ ቅድሚያ ከምትሰጣቸው ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ ሆና ትቀጥላለች ብለዋል።
ኔዘርላንድስ እንደ ሀገርም ሆነ በባለ ብዙ ወገን መድረክ የኢትዮጵያን የልማት ጥረት መደገፏን ትቀጥላለች ማለታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡