ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሩሲያ የዩክሬን የጦር መሳሪያ አውድመዋል ላለቻቸው ከ10 ሺህ በላይ ወታደሮቿ ጉርሻ ሰጠች

By Tamrat Bishaw

June 16, 2023

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ10 ሺህ በላይ የሩሲያ ወታደሮች “የጠላትን ዋና ዋና የጦር መሳሪያዎች በማውደማቸው እና በመማረካቸው” ጉርሻ ማግኘታቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሩሲያ ወታደሮች ታንክ፣ መድፍ፣ ተዋጊ ጄት ወይም ሌላ ወታደራዊ ቁሳቁስ በግል በመማረክ እና በማውደም ከ50 ሺህ እስከ 300 ሺህ ሩብል ወይም ከ600 እስከ 3 ሺህ 600 ዶላር ተከፍሏቸዋል መባሉን አር ቲ ዘግቧል።

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 7 ሺህ 64 ወታደሮች በአጠቃላይ 11 ሺህ 586 የዩክሬንን የጦር መሳሪያዎች እንዳወደሙ እና ጉርሻ እንደሚገባቸው የገለፀው ሚኒስቴሩ÷ በዚህ ዓመት አምስት ወራት ውስጥ የማረኩትና ያወደሙት የጦር መሣሪያ ብዛት ከ3 ሺህ 193 እስከ 4 ሺህ 415 እንደሚደርስ ተናግሯል።

የጦር ጄቶች እና ሄሊኮፕተሮችን በማውደማቸው ከፍተኛው ክፍያ ለአየር ኃይል እና ለአየር መቃወሚያ ባለሙያዎች መከፈሉም ነው የተገለፀው።

ሩሲያ ከዚህ ቀደም የአሜሪካን አብራምስ እና የጀርመንን ሊዮፓርድ ታንኮች እንዲሁም ኤፍ-16 የጦር ጄቶችን ለሚደመስስ አልያም ለሚማርክ የገንዘብ ሽልማት እንደምትሰጥ ማስታወቋ ይታወሳል፡፡