የሀገር ውስጥ ዜና

የኢጋድ እና የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ተቋም የሚኒስትሮች ጉባዔ ተጠናቀቀ

By Amele Demsew

June 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) እና የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ተቋም (ኢኤሲ) በስደተኞች ጉዳይ በዩጋንዳ ካምፓላ ሲያካሂዱት የነበረው የሚኒስትሮች ጉባዔ ዛሬ ተጠናቋል።

ለሁለት ቀናት በቆየው ጉባዔ ላይ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ አመራሮች፣ የስደተኞች ጉዳይ ባለሙያዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።

ጉባዔው በባለሙያዎች ደረጃ በተካሄደው ስብሰባ የቀረቡለትን አጀንዳዎች ላይ መምከራቸውም ነው የተገለጸው።

በሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም የተመራ የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን በመወከል በጉባዔው ላይ ተሳትፏል።

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በቀጣናው የስደተኞች ጉዳይን አስመልክቶ እያከናወኑ የሚገኘውን ስራ ለጉባዔው ማቅረቡም ነው የተነገረው።

ኢትዮጵያ ለስደተኞች ዘላቂ መፍትሔዎችን የሚያመጡ የተለያዩ ፖሊሲዎች እና መርሐ-ግብሮችን ቀርጻ በመተግበር ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እና ኃላፊነት በመጋራት መንፈስ የሰብዓዊ እና የልማት እርዳታን ሊያመጣጥን ይገባል ብለዋል።

የመፈናቀል መንስኤ ለሆኑ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ መገለጹን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡