የሀገር ውስጥ ዜና

ለወላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔ አስፈላጊ የምርጫ ግብዓቶች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ደርሰዋል- ምርጫ ቦርድ

By Melaku Gedif

June 18, 2023

አዲስ አበባ፣ሰኔ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በወላይታ ዞን ነገ በድጋሚ ለሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ አስፈላጊ የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች መድረሳቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

በነገው ዕለት በዞኑ በድጋሚ ለሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ቦርዱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጿል፡፡

በዞኑ በ12 የምርጫ ማስተባበሪያ ማዕከላት 1 ሺህ 812 የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን÷ በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች 9 ሺህ 60 የምርጫ አስፈፃሚዎች ወደ ተመደቡበት ጣቢያ መንቀሳቀሳቸው ተመላክቷል።

ከምርጫ አስፈፃሚዎች መካከል 5 ሺህ 212 የሚሆኑት ከአዲስ አበባ እንደመጡ የገለጸው ቦርዱ÷እነዚህም ከዚህ በፊት በሀገራዊ ምርጫ ተሳትፈው የተሻለ አፈጻፀም ያስመዘገቡ መሆናቸውን አንስቷል፡፡

ምርጫውን ለሚያስፈፅሙ አካላትም ቀደም ሲል አስፈላጊው ስልጠና መሰጠቱን ነው የቦርዱ መረጃ ያመላከተው፡፡

በአሀኑ ሰዓት ምርጫ አስፈፃሚዎቹም ሆኑ ሕዝበ ውሳኔውን ማካሄድ የሚያስችሉ ግብዓቶች  ወደየምርጫ  ጣቢያዎች መድረሳቸውን ቦርዱ አረጋግጧል፡፡

ሕዝበ ውሳኔው 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች በጋራ አንድ ክልል ለመመስረት የሚደረግ ሲሆን÷በወላይታ ዞን ጥር 29 ቀን 2015 ዓ. ም የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ላይ በተፈፀሙ የሕግ ጥሰቶች ሳቢያ መሰረዙ የሚታወስ ነው።

በማስተዋል  አሰፋ