አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ እና ቻይና ቀጣይ ግንኙነት የታይዋን ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ እና የማይጣስ ቀይ መሥመር መሆኑን የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ አስታወቁ፡፡
በታይዋን ግዛት ጉዳይ የሚነሱት ጥያቄዎች የቻይና የውስጥ ጉዳይ እንደሆኑም ነው ቺን ለአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የገለጹላቸው።
ቺን ጋንግ አሜሪካ የ“አንድ ቻይና” መርኅን እና ቀደም ሲል በጋራ ያወጧቸውን ሦስት መግለጫዎች እንድትታከብርም ጠይቀዋል፡፡
ታይዋን የቻይና ግዛት እንደሆነችና “የታይዋን ነፃነት” የሚባለውን ሐሳብ እንዳይደግፉም ነው ለአሜሪካው አቻቸው ያሳሰቡት፡፡
ቻይና ከአሜሪካ ጋር በሚኖራት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ቀጣይነት ያለው ፣ የተረጋጋ ፣ በትብብር እና ተከባብሮ በሠላም በመኖር ላይ የተመሠረተ መርኅ እንደምትከተልም ቺን መናገራቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡
የሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በኢንዶኔዢያ ባሊ የተደረሰውን ስምምነት ለመተግበር መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
ልዩነቶቻቸውንም በሰከነ መንፈስ ለማየትና በቀጣይ ውይይት እና ትብብር ለመፍታት መስማማታቸው ተመልክቷል።
በአጠቃላይ ሁለቱ ወገኖች በሁለትዮሽ ግንኙነቶቻቸው እና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ፣ ጥልቅ እና ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር በታላቁ የቻይና ሕዝብ አዳራሽ ተገናኝተው መክረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የቻይና አቋም በተመለከተ ብሊንከን ቀደም ብሎ በነበራቸው ውይይት ግልጽ መደረጉን በማንሳት፥ አሁን ላይ የሚጨምሩት ነገር እንደሌለ ጠቁመዋል።
ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር በኢንዶኔዢያ ባሊ የደረሱባባቸውን ሥምምነቶች ሁለቱም እንደሚያከብሩ ሥምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውሰዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚካሄድ ውይይት ሁልጊዜም በመከባበር ላይ የተመሠረተ መሆን አለበትም ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሺ፡፡
አንቶኒ ብሊንከንም የቻይና – አሜሪካን ግንኙነት በማደስ ረገድ አወንታዊ ሚና እንደሚኖራቸው ያላቸውን ዕምነት ገልጸውላቸዋል፡፡