የሀገር ውስጥ ዜና

20 ሚሊየን ወጣቶች የሚሳተፉበት የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አርብ ይጀመራል

By Alemayehu Geremew

June 21, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2015 የክረምት ወራት ሀገር አቀፍ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራም ከመጪው አርብ ጀምሮ እንደሚካሄድ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራሙ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ ኢዜአ ዘግቧል።

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፥ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 20 ሚሊየን ወጣቶች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ በሚሰጣቸው ሥምሪት ከ50 ሚሊየን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን ለማከናወን መታቀዱን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ፣ ደም ልገሳ፣ የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች የቤት ዕድሳት፣ የትራፊክና የመንገድ ደኅንነት አገልግሎትና የማጠናከሪያ ትምህርት ከሚሰጡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

ለአገልግሎቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር አገልግሎት የሚሰጡበትና ልምድ የሚቀስሙበት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በተያያዘም ሚኒስቴሩ ግጭት በደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ ለማልማት እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት ለመመለስ የሚያስችል የፕሮጀክት ስምምነት ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር ተፈራርሟል።

ፕሮጀክቱ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በተመረጡ ክልሎች እንዲሁም በ40 ወረዳዎች እንደሚተገበሩ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡