የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ለመፈተን ዝግጅት ተጠናቀቀ

By Alemayehu Geremew

June 21, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ለመፈተን ዝግጅት መደረጉን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የምዘናና ብሄራዊ ፈተናዎች ዳይሬክተር ክንፈ ፍስሃ ለኢዜአ እንደገለፁት ÷ ለዘንድሮ የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ተማሪዎችን ዝግጁ የማድረግ ስራ ተከናውኗል፡፡

ፈተናው በክልሉ በ75 ወረዳዎች ከሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ .ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥም ነው ያረጋገጡት፡፡

ለፈተናው የሚቀመጡ ተማሪዎች በ2012 ዓ. ም የመጀመሪያ መንፈቅ ትምህርት የተከታተሉና ዘንድሮ በተጀመረው ትምህርት የቀጠሉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

ተማሪዎቹ ከመደበኛ ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ በእረፍት ጊዜያቸው ሁሉ የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጣቸው መቆየቱን አብራርተዋል፡፡