አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ በልዩ ልዩ የወንጀል ድርጊቶች የተጠረጠሩ 32 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጎንደር ከተማ ጸጥታ ምክር ቤት ገለፀ።
ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የጎንደር ከተማ አስተዳደር የጀመረውን ህግ የማስከበር ስራ በማጠናከር በጎንደር እና በዙሪያዋ በሚገኙ፥ ቁስቋም፣ ወለቃ እና አርባባ በሚባሉ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ወንጀል የፈፀሙ 32 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በተለይም በቡድን በመደራጀት በተደጋጋሚ ጥይት በመተኮስ የአካባቢውን ሰላም በማወክ በተደጋጋሚ መንገድ በመዝጋት ዝርፊያ የፈጸሙ ይገኙበታል።
ከዚህ ባለፈም ለገበያ የሚወጡ አርሶ አደሮችን መንገድ በመዝጋት ክልከላ በማድረግ፣ በነብስ ማጥፋት የተጠረጠሩ፣ የእንስሳት ዝርፊያ የፈፀሙ፣ ነዋሪዎችን በማስፈራራት፣ ትንኮሳ የፈጸሙና ሰዎችን በማገት ተደጋጋሚ ወንጀል የተሰማሩ ይገኙበታልም ነው ያለው ምክር ቤቱ።
በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው ተጣርቶ በፍርድ ቤት የሚታይ መሆኑም ተገልጿል።
በነብዩ ዮሃንስ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።