የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል 2ኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በጌሌ ተራራ ተጀመረ

By Mikias Ayele

June 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ጉራዋ ወረዳ ጌሌ ተራራ ላይ ተጀምሯል፡፡

በመርሐ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረሀማን እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የፌዴራል እንዲሁም የክልሉ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩ ማስጀመሪያ ወቅት እንደተናገሩት÷ ለቀጣዩ ትውልድ የተመቸች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ለነገ ዛሬ መስራት ይገባል።

ተራሮች ድንጋይ የሚንከባለልባቸው ሳይሆኑ አትክልት የሚለማባቸው እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው÷ በክልሉ ዘንድሮ ከሚተከሉት ውስጥ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን የቡና ችግኝ እንደሚሆን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት የአርሶ አደሩ ህይወት እንዲቀየር ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡