የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ እየተካሄደ ያለው የኢንቨስትመንት ዘርፍ ውጤታማ ነው – አቶ ርስቱ ይርዳ

By ዮሐንስ ደርበው

June 26, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ከዚህ ቀደም ለእርሻ አገልግሎት ያልዋሉ ለም መሬቶችን ለአልሚ ባለሃብቶች በመስጠት እየተካሄደ ያለው የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተስፋ ሰጪ ውጤት ታይቶበታል ሲሉ አቶ ርስቱ ይርዳ ገለጹ፡፡

አቶ ርስቱ ይርዳ÷ በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ እና የአቶ ዳኜ ዳባን የግብርና ኢንቨስትመንት ስራ ጎብኝተዋል፡፡

ባለሃብቶቹ በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት አካባቢዎች የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎችን በማስፋፋት እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኤክስፖርት ምርቶችን በስፋት በማምረት ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ባለሃብቶቹ በቅባት እህሎች፣ በበቆሎ ምርጥ ዘር እና በፍራፍሬ ልማት ላይ እያካሄዱ ያለው የግብርና ኢንቨስትመንት ለአካባቢው ሕብረተሰብ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ እንዳስቻላቸውም ጠቁመዋል።

በጉራጌ ዞን በ5 ሺህ ሔክታር ላይ የቅባት ሰብሎችን እያለሙ ያሉት አቶ በላይነህ ክንዴ÷ የክልሉ መንግስት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ለዘይት ፋብሪካዎች በግብዓትነት የሚያገለግሉ ሰብሎች ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በጉራጌ ዞን ባለው የኢንቨስትመንት ልማት ከ200 በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን እና በሙሉ አቅም ወደ ስራ ሲገቡ ደግሞ ከ3ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጠር ጠቁመዋል፡፡

አቶ ዳኜ ዳባ በበኩላቸው ከአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በተጨማሪ የበቆሎ ምርጥ ዘር ችግርን ለመቅረፍ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣዩ ዓመት ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣ የአቮካዶ ምርት ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ለመላክ ማቀዳቸውን የደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡