የሀገር ውስጥ ዜና

በሶማሌ ክልል 2ኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተጀመረ

By Alemayehu Geremew

June 26, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

አቶ አገኘሁ ÷የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትና ችግርን ለመፍታት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።

የሶማሌ ክልል ም/ርዕሰ-መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው÷ በሶማሌ ክልል ባለፉት ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ ድርቅ መከሰቱን አስታውሰዋል፡፡

የሚከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት ለመከላከልም አካባቢን በደን መሸፈን ዋነኛ መፍትሔ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በድርቅና ጎርፍ አደጋ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ያለው ሚና የጎላ በመሆኑ ለመርሐ ግብሩ ትግበራ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡