የሀገር ውስጥ ዜና

ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በመቀጠም የሕዝቦችን አብሮነት ማጠናከሪያ ማድረግ ይገባል – ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

By Alemayehu Geremew

June 26, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ለበጎ ዓላማ በማዋል የሕዝቦችን አብሮነት ማጠናከሪያ ማድረግ ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የኢንተርኔት አገልግሎት ተደራሽነትን ተከትሎ ማሕበራዊ ሚዲያው ተጽዕኖ ፈጣሪና ቀዳሚ የሕዝብ የመገናኛ አማራጭ መሆኑን አንስተዋል።

ይህን ተከትሎም ተፈላጊ መረጃዎችን በፍጥነት በማድረስ በሕዝብ ሕልውና ውስጥ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም ይህ የእድገት አንዱ የስልጣኔ መገለጫ የሆነው ማህበራዊ ሚዲያ ለኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አቅም በመሆኑ ለሰላም፣ ለልማትና ለሀገር ግንባታ መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በአንጻሩ ማሕበራዊ ሚዲያው ለሁለንተናዊ እድገት ሚናው የጎላ ቢሆንም በአግባቡና በሰለጠነ መንገድ መጠቀም ካልተቻለ እጅግ የከፋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚያስከትል አስገንዝበዋል፡፡

በተለይም አሁን አሁን ማህበራዊ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ በመጠቀም የተዛቡ፣ በጥላቻና በልዩነት የተሞሉ፣ መሰረት ቢስ ወሬዎችን በማሰራጨት በሕዝብ መካከል ልዩነት በመፍጠር የግጭትና ሁከት መቀስቀሻ መሳሪያ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

ከልዩነት እና ጥላቻ ደግሞ ጥፋት እንጅ የሚገኝ ትርፍ የለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ ዓላማ በማዋል የህዝቦችን አብሮነት፣ ወንድማማችነት፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር የባህልን ማጠናከሪያና ማቀራረቢያ መሳሪያ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በአማራ ክልል ዘርፉን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም በጋራ የተንቀሳቀሱ ወጣቶችና የበጎ ሃሳብ ባለቤቶች መልካም ስራዎችን ለአካባቢያቸው ሕዝብ ማበርከታቸውን አውስተዋል፡፡

በዚህ ረገድ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ለበጎ ተግባር በመጠቀም አርዓያ ለሆኑ ወጣቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡