አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የረመዳን ወር ፆምን ምክንያት በማድረግ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ ኑሮ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
በክፍለ ከተማው ከ10 ወረዳዎች ለተውጣጡ 200 አቅመ ደካሞች እና በዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ አባወራዎች ማዕድ የማጋራት የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ተካሂዷል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት ሰጭ አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴ እና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ይታያል ደጀኔ የምግብ ቁሳቁስ ድጋፉን አበርክተዋል።
ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት ህዝባችን በችግር እና በሀዘን ጊዜ ይደጋገፋል፣ ያለውን ይሰጣል፣ እርስ በራሱ ይተሳሰባል ይህ ባህል በእጅጉ የሚያኮራ እና የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫም ነው ብለዋል።
ህዝበ ሙስሊሙም በረመዳን ወቅት ለሌላቸው በመስጠት እና በማብላት የሚታወቅበትን ባህል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ይታያል ደጀኔ በበኩላቸው ፈተናዎች በበዙበት በአሁኑ በመተጋገዝ አስቸጋሪውን ጊዜ ማለፍ ስለሚገባ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።