የሀገር ውስጥ ዜና

ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሀ በዓልን ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በመርዳት እንዲያሳልፍ ጥሪ ቀረበ

By ዮሐንስ ደርበው

June 27, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2015፣ (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሀ በዓልን ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በመርዳት እንዲያሳልፍ የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ፡፡

ምክር ቤቱ 1 ሺህ 444ኛውን የኢድ አል አድሀ (አረፋ) በዓል ምክንያት በማድረግ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እና የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ ሱልጣን አማን ኤባ በሰጡት መግለጫ÷ “ዒድ አል አድሀ ነቢዩ ኢብራሂም ለጌታው የነበረውን ፍጹም እምነት፣ በቆራጥነት ያሳየበት ልዩ ቀን ነው” ብለዋል፡፡

ፈጣሪ አላህ ልጅህን መሥዋዕት አቅርብልኝ ብሎ በጠየቀው ጊዜ ኢብራሂም አንድዬ ልጁን፣ እስማኤልን ወደ መሠዊያው መውሰዱን አስገንዝበዋል፡፡

ፈጣሪም የኢብራሂምን ፍጹም እምነት ተመልክቶ፣ ሙክት እንደሰጠውና በልጁ ምትክ ሙክቱ ስለተሰዋ የሚከበር በዓል መሆኑን በማንሳት በዚህም ምክንያት “የመሥዋዕት በዓል” እየተባለ እንደሚጠራ አስረድተዋል፡፡

ሕዝበ ሙስሊሙ ታላቁን የአረፋ በዓል ሲያከብር አቅመ ደካሞችን በመጠየቅ፣ የተራቡትን በማብላት፣ የታረዙትን በማልበስ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

ሕዝበ ሙስሊሙ ነገ በድምቀት የሚከበረውን ታላቁን የኢድ አል አድሀ (አረፋ) በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጠይቀዋል።

በዓሉ በመዲናዋ ሶላትን ጨምሮ በተለያዩ ሐይማኖታዊ ክዋኔዎች እንደሚከበር ተገልጿል፡፡

ነገከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ በአዲስ አበባ ስቴድየም ሶላቱ እንደሚጀመርም ነው የተመለከተው፡፡

በሳሙኤል ወርቃየሁ እና ዳዊት ደያሳ