አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “አሸዋ ቴክኖሎጂስ” አዳዲስ የስማርት ቴክኖሎጂ ውጤቶቹን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
ቴክኖሎጂዎቹ ለአነስተኛ እና ጥቃቅን እንዲሁም ለከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሆኑና ለዘመናት የቆየውን ልማዳዊ አሰራር የሚቀይሩ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
የስማርት ቴክኖሎጂ ውጤቶቹ ሀገር በቀል ሲሆኑ÷ ከረዥም ጊዜ ሙከራ በኋላ ይፋ እንደተደረጉ ነው በማስጀመሪያ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ የተነገረው።
የስማርት ቴክኖሎጂው በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲበለጽግ የተደረገው÷ የ “ኢ አር ፒ” አገልግሎትን ጨምሮ የኦንላይን ግብይት የአሰራር ሥርዓት፣ የሠራተኞች መቆጣጠሪያ፣ የደንበኛ ግንኙነት አስተዳደር ፕሮጀክቶችን በአንድ ቦታ በቀላሉ ለማስተዳደር የሚያግዙ በመሆናቸው ነው ተብሏል፡፡
አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን አክስዮን ማኅበር÷ በኢትዮጵያ ሁሉ ያሉ ቢዝነሶችን በቴክኖሎጂ እገዛ የበለጠ ምርታማ ፣ ትርፋማ እና የተደራጁ ለማድረግ በኢ-ኮሜርስ፣ በኢ- ለርኒንግ፣ በሎጂስቲክስ፣ በፊንቴክ እና በአጠቃላይ 11 የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ በሥራ ላይ የሚገኝ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ድርጅት ነው።
“ሶፍትዌሮቹ”÷ ከዚህ ቀደም ከሌሎች ሀገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝተው አገልግሎት ላይ ሲውሉ የነበሩትን ቴክኖሎጂዎችን እዚሁ ሀገር ውስጥ በማበልጸግ የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት ያግዛሉም ነው የተባለው።
ይፋ የተደረጉት የቴክኖሎጂ ውጤቶች የንግድ ድርጅቶች ትርፋማነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እንደሆኑም ነው የአሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ዳንኤል በቀለ ገልጸዋል።
በታሪኩ ወ/ሰንበት