አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ሰላም ለማፅናትና የተሻለች ሀገርን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ሁሉም ዜጎች በሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉና ለስኬቱ የበኩላቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመጪው ዓመት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችለውን ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑ ይታወቃል።
ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ የቅራኔና የግጭት መነሻ የሆኑ የፖለቲካ ስብራቶች መፍትሔ እንዲያገኙ፣ ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር የሚያስችል ምክክር ለማካሄድ የአመቻችነት ስልጣን ተሰጥቶት ወደ ስራ ገብቷል።
ለዚህም በሀገሪቱ በተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ ተሳታፊዎችን የመለየት እና ህዝቡ የሚያነሳቸውን አጀንዳዎች በማሰባሰብ ላይ መሆኑን ገልጿል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አረዓያ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የተሳታፊ ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራው ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ በየወረዳው እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሃይማኖት ተቋማት፣ የመምህራን ማህበር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ሌሎች ተባባሪ አካላት ተመርጠው ሂደቱን የማገዝና አካታችነትና ገለልተኛነቱን የመከታተል ስራም እየሰሩ ነው ብለዋል።
በዚህም በድሬደዋ፣ በሀረር፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች፣ በጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳን የመቀበል ስራ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የ2015 በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት በሌሎች ክልሎች በምክክሩ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮችንና መሰረታዊ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ስራ እንደሚከናወንም ጠቅሰዋል።
የዝግጅት ስራዎችን በዚህ በጀት ዓመት በማጠናቀቅ በቀጣይ ዓመት ዋናውን ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ የሚያስችል መሰረት ለመጣል እየተሰራ መሆኑን በመጠቆም።
ፕሮፌሰር መስፍን አክለውም ለመጪው ትውልድ ሰላሟ የተረጋገጠ እና የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በመሆኑም መንግስት፣ የታጠቁ ኃይሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት አባቶች በአጠቃላይ ሁሉም ዜጋ ለምክክሩ ስኬታማነት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግና ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።