አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የት/ቤቶች መሰረተ ልማት የማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ የፊታችን እሑድ በይፋ እንደሚጀመር ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ በመላው ሀገሪቱ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚደረገውን የንቅናቄ መርሐ-ግብር አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ወቅት÷ የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በንቅናቄው ከ50 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል መታቀዱ ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
ሀገር አቀፍ ንቅናቄው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚሰሩ ስራዎችን የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ያሉ ትምህርተ ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ÷ በሚቀጥሉት አምሰት ዓመታት የትምህርት ቤቶቹን ደረጃ የማሻሻል እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
በአዳነች አበበ