አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትምህርት ላይ የምንሠራቸው ሥራዎች ወጣቶቻችን በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ለመጓዝ የሚያስፈልጋቸውን ዕውቀት እና ክህሎት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት የመጀመሪያው ልዩ ጉባዔ ላይ እየሳተፉ ነው።
በጉባዔው ላይም ባስተላለፉት መልዕክት÷ኢትዮጵያ በትምህርት አቅርቦት ውስጥ አካታችነትን ለማጎልበት በምታደርገው ጥረት የሥርዓተ ጾታ ክፍተቱ እንዲዘጋና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን እንዲያገኙ የሚቻለው ሁሉ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በትምህርት ላይ የምንሠራቸው ሥራዎች ወጣቶቻችን በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ለመጓዝ የሚያስፈልጋቸውን ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነውም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ለአርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች መሠረተ ልማት እና የትምህርት አገልግሎቶችን ማስፋፋት፣ መደበኛ ያልሆነ ትምህርት እና የሥልጠና መርሐ ግብሮችን ለዐዋቂዎች መስጠት እና የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሆኑን ማረጋገጥ ከሚሠሩ ዋና ዋና ሥራዎች ጥቂቶቹ ናቸው ብለዋል።