የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ጨምሮ ለደም ለጋሾች እውቅና ሰጠ

By Shambel Mihret

June 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ጨምሮ ለደም ለጋሾች እውቅና ሰጥቷል፡፡

እውቅናና ምስጋናው የተሰጠው÷ በመደበኝነት ደም ለሚለግሱና ለሚያስተባብሩ ግለሰቦች፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ የበጎ አድራጎት ማኅበራት፣ የሚዲያ ተቋማት እንዲሁም ለሌሎችም አካላት ነው።

የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ÷ ደም ማለት ሕይወት በመሆኑ ሕይወት እየሰጡ ለሚገኙ አካላት ምስጋና ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች፣ በወሊድ፣ በትራፊክ አደጋና መሰል በሽታዎች ምክንያት በርካቶች ደም እንደሚያስፈልጋቸው አስገንዝበዋል፡፡

ፍላጎቱን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት መደበኛ ደም ለጋሾች የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ከፍተኛ የደም እጥረት በመኖሩ ሁሉም ደም በመለገስ ሕይወትን ሊያድን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በቀጣዮቹ ክረምት ወራት በሚካሄደው ደም የመለገስ መርሐ ግብር  ሁሉም እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በቅድስት አባተ