የሀገር ውስጥ ዜና

ሙስናን በሐቀኝነት እንጂ በማስመሰል ልንዋጋው አንችልም – ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር)

By ዮሐንስ ደርበው

June 30, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሙስናን በሐቀኝነት እንጂ በማስመሰል ልንዋጋው አንችልም ሲሉ የሥነ -ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የፌዴራል መንግስት አስፈፃሚ አካላት የሥነ-ምግባር ክትትል እና የጥቅም ግጭትን ለመከላከልና ለማስወገድ በፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ሙስና እንደ ሀገር ትልቅ አደጋ ደቅኖ ያለ የሰላምና የልማት እንቅፋት ነው ብለዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመከላከልም መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በዋነኛነት የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ሙስናን እንዲዋጉ ታስቦ ረቂቅ ደንቡ መዘጋጀቱንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የሥነ- ምግባር ክትትል እና የጥቅም ግጭትን ለመከላከል ለአስፈፃሚው አካል የወጣና የሚመራበት ደንብ አለመኖሩ በራሱ የፈጠረው ችግር መኖሩን ጠቁመው÷ ይህን ለማስተካከልም ረቂቅ ደንቡ ያግዛል ነው ያሉት፡፡

በመድረኩ የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በበረከት ተካልኝ