የሀገር ውስጥ ዜና

ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሀገር አቀፍ የጤና አውደ ርዕይን ጎበኙ

By ዮሐንስ ደርበው

June 30, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፕላንና ልማት ሚንስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እና በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) የተመሩ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ቡድኖች ሀገር አቀፍ የጤና አውደ ርዕይን ጎብኝተዋል።

ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት÷ የጤናው ዘርፍ የእድገት መለኪያዎች በቴክኖሎጂ የተደገፉ መሆናቸው ጠንካራ የጤና ስርዓት ለመዘርጋት የሚደረገውን አገራዊ ርብርብ ያፋጥናሉ፡፡

ይህንንም በአውደ ርዕዩ በቀረቡ ማሳያዎች ተመልክተናል ማለታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) በተመለከቱት የጤናው ሴክተር በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መደነቃቸውን ገልጸዋል፡፡

በዘርፉም የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውን ጠቁመው በጤናው ዘርፍ ኢንቨስት ማድረግ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ባለሀብቶች ኢንቨስት በማድረግ አገራቸውንና ወገኖቻቸውን እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል።

ሀገር አቀፍ የጤና አውደ ርዕዩ በቀጣይ ሳምንታትም ለጉብኝት ክፍት እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡