የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ

By Alemayehu Geremew

July 03, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ግንኙነታቸውን በይበልጥ ለማሳደግ ተስማምተዋል፡፡

በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ የተመራ ልዑክ በደቡብ ኮሪያ የጊዮንግሳንግቡክ ዶ ግዛትን ጎብኝቷል፡፡

ከግዛቷ አስተዳዳሪ ቼኦል ው ሊ ጋርም በሁለትዮሽ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡

በውይይታቸውም በግዛቲቷ እና በኢትዮጵያ መካከል በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ትስስር መፍጠር እና ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል፡፡

ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ዘመናትን የተሻገረ ታሪክ እንዳላቸው ያስገነዘቡት አምባሳደር ደሴ÷ ይህንን አኩሪ ታሪካቸውን በልማቱ ዘርፍም እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡

የጊዮንግሳንግቡክ ዶ ግዛት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ክልሎች ጋር በአጋርነት ብትሠራ ተጠቃሚ እንደምትሆን አስረድተዋል፡፡

ቼኦል ዉ ሊ በበኩላቸው ÷ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ክልሎች ጋር በትብብር መሥራት በሚችሉባቸው ዘርፎች ላይ በጥምረት የመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው አረጋግጠዋል፡፡

በተጨማሪም አምባሳደር ደሴ ዳልኬ እና ልዑካቸው ÷ በግዛቷ አቅራቢያ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ከንቲባዎች ጋር መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በግዛቲቱ አቅራቢያ ከሚገኙ ኩባንያዎች ፕሬዚዳንቶች እና ሥራ አስፈጻሚዎችን ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡