የሀገር ውስጥ ዜና

በአንዳንድ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተመላከተ

By Amele Demsew

July 04, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሚያገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳስቧል፡፡

ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች የአፈር መሸርሸር እንዳይከሰት እንዲሁም ውሃ በማሳ ላይ በመተኛት ጉዳት እንዳያደርስ የጎርፍ መከላከያ እርከኖችና ማፋሰሻዎችን መስራት እንደሚገባ ነው ኢንስቲትዩቱ ያስታወቀው፡፡

በመጪው ሐምሌ ወር በኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች የክረምቱ ዝናብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ሆሮጉድሩ፣ ቄለም ወለጋ፣ አርሲና ባሌ ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ ተገልጿ፡፡

በተመሳሳይ÷ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ ባህርዳር ዙሪያ፣ አዊ ዞን፣ ሰሜን ሸዋ ዞኖች፣እንዲሁም በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ደቡብ ክልሎች ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል፡፡

በተጨማሪም÷የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛኛው ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ ከኢኒስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች፣ በአፋር ክልል የሚገኙ ዞኖች፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ ድሬዳዋ፣ የሶማሌ ክልል ሰሜናዊ ዞኖች፣ ምስራቅና ደቡብ ትግራይ በብዙ ቦታዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡

የክረምቱ ዝናብ የመኸር እርሻ ለተጀመረባቸው አካባቢዎች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ነው የተጠቆመው፡፡

በዝናብ አጠር አካባቢዎችም ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባም ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡