አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአየር ንብረት ለዉጥን የሚቋቋሙና በዘርፉ ያሉ መልካም ዕድሎችን መጠቀም የሚያስችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡
“የግሉ ዘርፍ የአየር ንብረት ለዉጥን በመከላከልና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን መጠቀም” በሚል ርዕስ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከ”ግሎባል ግሪን ግሮዉዝ ኢንስቲትዩት” ጋር ውይይት አካሄዷል፡፡
በውይይቱ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳንዶካን ደበበ ÷የአየር ንብረት ለዉጥ ጉዳይ በአሥር ዓመቱ መሪ ዕቅድ ላይ በትኩረት መቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡
የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለዉጥ ጉዳይ የመንግስት ኃላፊነት ብቻ አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ÷ በአረንጓዴ ቴክኖሎጂዎች እና መሰል ዘርፎች ላይ የግሉ ዘርፍ ሊሳተፍባቸው የሚያስችሉ ዕድሎች መኖራቸዉን አንስተዋል፡፡
የ”ግሎባል ግሪን ግሮዉዝ ኢንስቲትዩት” የኢትዮጵያ ተወካይ ዳንዔል ኤኬቹኮ በበኩላቸዉ ÷ የአየር ንብረት ለዉጥና ተከትሎ የሚመጣዉ ቀዉስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራች መሆኑን ያነሱት ተወካዩ ÷ ሀገሪቷ በተለያዩ ዓለምአቀፋዊ መድረኮች የሕዝቦቿንና የአፍሪካን ድምጽ እያሰማች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአየር ንብረት ለዉጥን በመከላከል ረገድ የካርቦን ልቀትን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እና በአረንጓዴ ልማት ላይ ኢንቨስትመንት ማድረግ ከግሉ ዘርፍ የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በውይይቱ የንግድና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ፣ ከግብርና አመራችና ላኪ ኩባንያዎችና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን መሳተፋቸውንም ከፕላንና ልማት ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡