አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምግብ ዋስትናዋ የተረጋገጠባት ከተማን ለመገንባት ሁሉም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ላይ ሊሳተፍ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ ገለፁ።
የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሠራተኞች እና በከተማዋ የሴፍቲኔት ተተቃሚዎች “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ሐሳብ በየካ ክፍለ ከተማ የአረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡
በዚሁ ወቅት አቶ ጃንጥራር ዓባይ እንዳሉት÷ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት ለመገንባት ችግኝ መትከል ዋነኛ መፍትሄ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማን የአረንጓዴ ሽፋን ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ ቢሮው የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ያበረክታል ማለታቸውን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡