አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ክረምት ተጨማሪ 2 ሚሊየን ሄክታር በሰብል እንደሚሸፈን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
በዚህ ወቅትም በተያዘው ክረምት ተጨማሪ 2 ሚሊየን ሄክታር በሰብል እንደሚሸፈን ጠቅሰው፥ 15 ሚሊየን ሄክታር ለመጀመሪያ ጊዜ ይታረሳል ብለዋል።
አያይዘውም ምርት በውድ ዋጋ ከተመረተ ዝቅተኛ ገንዘብ ያላቸውን ሰዎች እንደሚጎዳ በማንሳት ለማዳበሪያ 21 ቢሊየን ብር ድጎማ መሰጠቱን ጠቁመዋል።
15 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ገደማ ማዳበሪያ እንደተገዛና የተፈጥሮ ማዳበሪያን ለማስፋፋትም 178 ሚሊየን ኩቢክ የሚጠጋ የተፈጥሮ ማዳበሪያም መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡
በአፈር አሲዳማነት የተበሉ መሬቶችን በኖራ በማከም በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉና እነዚህም ምርታማነት ለማስፋት እንደሚያግዙም አመላክተዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም በአፈር አሲዳማነት የተመታ 7 ሚሊየን ሄክታር የሚጠጋ መሬትን ለማከም 5 የሚሆኑ የኖራ ፋብሪካዎች መከፈታቸውንም አንስተዋል።
ምርታማነትን ማብዛትና የሀገርን እድገት ማስቀጠል ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢንዱስትሪ በኢኮኖሚ ውስጥ 28 በመቶ ድርሻ አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ዘርፉ በዚህ አመት 8 ነጥብ 2 በመቶ እድገት እንደሚያመጣ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 160 የሚሆኑና ስራ ላይ ያልነበሩ ፋብሪካዎች ስራ እንዲጀምሩ መደረጉንም ጠቅሰው፥ በእነዚህ ፋብሪካዎች የምርትና ምርታማነት እድገት እንደሚጠበቅም ነው ያነሱት።
ከኃይል አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ ዘንድሮ የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀማችን በ15 በመቶ ማደጉን አስረድተዋል።
በየሻምበል ምሕረት