አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር እና በሰላማዊ መንገድ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገለፁ፡፡
የቢሮ ኃላፊው በበጀት ዓመቱ የሰላምና የልማት ጉዳዮችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም÷በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአንድአንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት መፈናቀሎችና ህገወጥ ተግባራት በመከሰታቸው ምክንያት የሰላም እጦት እንደነበር አንስተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች መስተዋላቸውን ገልፀዋል፡፡
የሰላም እጦት መኖር ደግሞ ልማትን ያደናቅፋል ያሉት ሃላፊው ÷ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን ህዝብና መንግስት በጋራ ሊፋታቸው አንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
የአማራ ህዝብ ጥያቄ የሆኑት የማንነት፣ የተሳሳተ ትርክትና የህገመንግስት መሻሻል፣ የወሰንና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር የሚመለሱት በሰላማዊ መንገድ ነው ብለዋል።
ክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የሰላም እጦቶችም የክልሉን የልማት እንቅስቃሴ ወደኃላ እንዳይጎትቱ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የክልሉን ልማት እንቅስቃሴ በተመለከተ በሰጡት መግለጫም÷በክልሉ በ2015/2016 የመኸር ምርት የግብርና ልማት ስራዎች በማከናወን 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ይታረሳል ብለዋል።
ለዚህም በክልሉ 9 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል የአፍር ማዳበሪያ ለመኸር እርሻ እንደሚያስፈልግ እና እስካሁን 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ መፈፀሙን አስረድተዋል፡፡
በጳውሎስ አየለ