የሀገር ውስጥ ዜና

ሕገ-ወጥ ካርታ አዘጋጅተው የመንግስት ቦታ እንዲወሰድ አድርገዋል የተባሉ 3 ተከሳሾች በቀረበባቸው የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

By Melaku Gedif

July 07, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሸገር ከተማ ቡራዩ ክ/ከተማ አራት የመንግስት ቦታዎችን በተጭበረበረ መንገድ ካርታ አዘጋጅተው እንዲወሰዱ አድርገዋል የተባሉ ሶስት ተከሳሾች በቀረበባቸው ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ፡፡

የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ዛሬ በዋለው ችሎት ነው ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠው፡፡

ተከሳሾቹ በግል ስራ ይተዳደራል የተባለው 1ኛ ተከሳሽ አማኑ ግዛው እና የቡራዩ ክፍለ ከተማ የመሬት አስተዳደር የካርታ ዝግጅት ባለሙያዎች ናቸው የተባሉት 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ዳንዲ ቀና እና ሳኒ ግርማ ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ላይ ባቀረበው ክስ ላይ እንደተመላከተው፥ ተከሳሾቹ በጥቅም በመመሳጠር የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በሸገር ከተማ በቡራዩ ክ/ከተማ መሬት አስተዳደር የካርታ ዝግጅትና አረጋጋጭ ባለሙያ ሆነው ሲሰሩ ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም በይዞታነት ያልተመዘገቡ 4 የተለያዩ ቦታዎችን በሀሰተኛ ሰነድ ተጠቅመው በቡራዩ መልካ ገፈርሳ በተባለ አካባቢ በሽር አህመድ በሚል ስም ካርታና የቦታ ፕላን በሕገ-ወጥ መንገድ አዘጋጅተው ለ1ኛ ተከሳሽ መስጠታቸው በክሱ ላይ ተብራርቷል፡፡

ይህንን በሀሰተኛ ሰነድ የተሰጠ ቦታን አንደኛ ተከሳሽ የእኔ ነው በማለት ለሌሎች አካላት በሽያጭ ሲያስተላልፍ እንደነበርም በክሱ ተጠቅሷል።

እንደ አጠቃላይ በዚህ በተዘጋጀ ካርታና ፕላን በእያንዳንዱ 200 ካሬ ሜትር ይዞታ ሆኖ የተሰጠ ሲሆን፥ በዚህ መልኩ የመንግስት ባዶ ቦታን በሕ-ገወጥ መንገድ በመውሰድ መንግስት ሊያገኝ የሚገባውን 4 ሚሊየን 243 ሺህ 496 ብር አሳጥተዋል በማለት ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አስፍሯል።

አንደኛው ክስ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን ክሱም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር ሶስት በመተላለፍ የሚል ነው።

2ኛው ክስ ደግሞ በ2ኛ እና በ3ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን፥ ይህም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ/ለ እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 2 /ሀ ስር የተደነገገውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት በዋና ወንጀል አድራጊነት የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በዚህ የተሳትፎ ደረጃ ተጠቅሶ የቀረበው የሙስና ወንጀል ክስ ዝርዝር በችሎት እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ ተከሳሾቹ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ሰባት የሰው ምስክሮች እና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም ዛሬ በዋለው ችሎት የምስክሮችን ቃልና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ እያንዳንዳቸው በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ችሎቱ ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ ካላቸው ለመጠበቅ ለሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ